Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

በሲዳማ ክልል የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ዘመቻ ተጀመረ።

የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 18/2018 ዓ.ም

አምስተኛው ዙር የተቀናጀ የፓሊዮ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ክብርት ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ እና የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የማህበራዊ ዘርፍ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አየለች ሌዳሞን ጨምሮ፣የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የክልል ጤና ቢሮና የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶች፣ባለድርሻ አካላት ፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ማህበረሰቡ በተገኙበት በዛሬው ዕለት በወንዶገነት ወረዳ አሩማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ላይ በይፋ ተጀምሯል።

ዘመቻውን ለማስጀመር የተገኙት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በመልዕክታቸው የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በህፃናት ላይ ዘላቂ የአካል ጉዳት ብሎም ሞት የሚያስከትል አደገኛ በሽታ መሆኑን ጠቁመው ፤ ይህንንም ለመከላከል ከዛሬ ጀምሮ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆናቸው ህፃናት ለተከታታይ አራት ቀናት የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) ክትባት ስለሚሰጥ ወላጆች/አሳዳጊዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ አንድም ህፃን ሳይከተብ እንዳይቀር ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ሀላፊዋ አያይዘውም በክልሉ 1,150,553 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሀምሳ ሺህ አምስት መቶ ሀምሳ ሶስት ) ያህል ህፃናት እንደሚከተቡ ጠቁመው፣ክትባቱም ቤት ለቤት እንደሚካሄድ አሳውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው የፖሊዮ መከላከያ ክትባት የመስጠት ዋና አላማውን ሲገልፁ ችግሩ በሀገራችን በተለያዩ አጎራባች ክልሎች በመከሰቱ ይህንን ችግር ለመከላከል ደግሞ ክትባት እጅግ ወሳኝ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ህፃናቱ ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም እድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች ከሆናቸው በተጠቀሱት ቀናቶች መከተብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

መጋቢት 18/2018ዓ/ም

ሀዋሳ

ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

Web site: https://www.sphi.gov.et/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *