Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የጂኖሚክ ምርምር አቅም ለማሳደግ ስትራቴጂካዊ የግብዓት ርክክብ አደረገ

——————————–

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የጤና ደህንነትና የወረርሽኝ መከላከል አቅም በምርምር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ስትራቴጂካዊ የምክክርና የግብዓት ርክክብ መድረክ ከክልል አቻ ተቋማት ጋር አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ እና የተላለፊ በሽታዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገመቹ ታዳሰ የጀኖሚክስ እድገትን አስመልክቶ ሰፊ ማብራርያ አድርገዋል፡፡ በመድረኩ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከሲዳማ እና ከትግራይ ክልሎች የተወከሉ የጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ይህ የምክክር መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን የጂኖሚክ ጥናትና ምርምር ስራዎች አሁን ላይ ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም እና ተቋማዊ ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በዚሁ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ተቋማዊ አቅምን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና የምርምር አቅምን ለማሳደገግ የሚያስችሉ፣ በ1.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገዙ የጂኖሚክ ጥናትና ምርምር ግብዓቶች ለክልል ተቋማቱ ርክክብ ተደርጓል። ይህ ከፍተኛ በጀት የተመደበለት የድጋፍ ስራ የግሎባል ፈንድ (Global Fund) አካል ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍን ያቀፈ ነው። ከዚህ ውስጥ 5.3 ሚሊዮን ዶላር በለይ የሚሆነው በቀጥታ ለክልል የጂኖሚክ ማዕከላት ግንባታና አቅም ማጠናከሪያ እንዲውል የተመደበ ሲሆን፣ ቀሪው 3.6 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተግባራት የሚውል ይሆናል።

ርክክብ የተደረገባቸው ግብዓቶች እንደ Illumina NextSeq 2000 supplies ያሉ ዘመናዊ የዘረመል መመርመሪያ መሣሪያዎችን የሚያንቀሳቅሱ ወሳኝ ግብዓቶችን ያካተቱ ናቸው። ተሳታፊዎቹም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙትን የላቁ የጂኖሚክና የባዮ ኢንፎርማቲክስ ማዕከላትን በመጎብኘት በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በዝርዝር ተመልክተዋል። ይህ የተቀናጀ ጥረት በሀገሪቱ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን አስቀድሞ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ታምኖበታል።

www.ephi.gov.et/news

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *