Skip to content 
ሕዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገራችን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጰያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ባወጡት ወቅታዊ መግለጫ ማሳወቃቸዉ ይታወቃል።
ከዚያም ዕለት ቀደም ብሎ በ29/02/2018 ዓ.ም ከጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕሙማን ለተሻለ የሕክምና አገልግሎት ወደ ሀዋሳ ኮምፕሪሄንሲቭ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመምጣታቸዉ ጋር ተያይዞ ከህዳር 3/2018 ዓ.ም ጀምሮ የሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል (PHEOC) ስራዉን በይፋ በመጀመር ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወረርሹኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በመሆኑም በክልላችን የማርበርግ ቫይረስ በሽታ የምላሽ ስራዎች ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስከ 29/04/2018 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ በበሽታዉ የተጠረጠሩ 2200 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከጂንካ ከመጡ ታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበረዉ አንድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ በበሽታው መያዙን ለማረጋገጥ ተችሏል።
በተጨማሪም በሽታዉ ከተገኘባቸዉ ታማሚዎች ጋር ንክኪ ያላቸዉ በድምሩ 97 ተጠርጣሪዎች ለ21 ቀናት በለይቶ ማቆያ እና በሕክምና ማዕከል ላይ ለ21 ቀናት ክትትል እና አስፈላጊዉ ድጋፍ ከተደረገላቸዉ በኃላ ወደየቤታቸዉ ተመልሰዋል።
ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር እና የሕብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅ የክስተት አስተዳደር ስርዓትን በማጠናከር የተቀናጀ የቅኝትና ምላሽ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን የላቦራቶሪ ምርመራ በክልላችን በሀዋሳ ከተማ የማስጀመር፣ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን አቋቁሞ የመመደብ፣ የለይቶ ማቆያ እና ማከሚያ ማዕከላትን የማቋቋም፣ የሚያስፈልጉ የህክምና ግብኣቶችንና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁሶችን የሟሟላት፣ ለበሽታዉ መከላከያ እና ህክምና የሚዉሉ መድሃኒቶችን የማቅረብ እና የቅኝትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከክልላችን ከ4ኛ ዙር የፖሊዮ ዘመቻ ጋር በማቀናጀት ቤት ለቤት ተሰርቷል።
በመውጫና መግቢያ ስድስት ኬላዎች ልየታዎችን በማካሄድ ለ4.3 ሚሊዮን ተጓዦች ልየታ የተደረገ ሲሆን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሕዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በጥንቃቄ እንዲከበሩ ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በሀገራችን የማርበርግ በሽታ ቅኝትና ምላሽ መምሪያ መሰረት ወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወጀው የመጨረሻው የማርበርግ ታማሚ ከነበረበት በ42 ቀናት ውስጥ ሌላ ተጨማሪ በበሽታው የተያዘ እንዲሁም ህይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩ ሲረጋገጥ ሲሆን፤ በክልላችን የመጨረሻው የማርበርግ ታማሚ ከተለየ 43 ቀናት የሞላ ስለሆነ፤ ወረርሽኙ ከታህሳስ 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ የክልላችን ህብረተሰብ የጤና ስጋት አለመሆኑን እያሳወቅን ይህ ወረርሽኝ በአጠረ ጊዜ መቆጣጠር የተቻለዉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ባደረገዉ ርብርብና ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም ተቀናጅቶ በመሥራት በመሆኑ በዚህ ወረርሽኝ ምላሽ ላይ የተሳተፉ እና እየተሳተፉ ያሉ የጤና ባለሙያዎቻችን፣ ጤና ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣Armauer Hansen Research Institute (AHRI)፣ የዘርፉ አመራሮች፣ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ መያድ፣ አጋር አካላትን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን፡፡
ይሁን እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጨረሻ የማርበርግ ታማሚ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ 42 ቀን ስላልሞላ የሚከተሉት ቁልፍ የህብረተሰብ ጤና ምላሽ ተግባራትን በትኩረት የምንሰራ ይሆናል፤
• በማህበረሰብ እና በጤና ተቋማት ውስጥ የተጠናከረ የበሽታ ቅኝትና ክትትል ማካሄድ፤
• የበሽታው ምልክት የሚታይባቸውን ተጠርጣሪዎች የመለየት፣ የማሳወቅና በአፋጣኝ የጤና ክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ፤
• በሁሉም የጤና ተቋማት የበሽታውን ስርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፤
• የህብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋት ተግባቦትን እና የማህበረሰብ ተሳትፎን በየደረጃው ማጠናከር ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ማንኛውም መንስኤው ያልታወቀ ሞት ሲከሰትና የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምልክቶችን የሚመስሉ አጠራጣሪ ሁኔታዎች በህሙማን ላይ ሲከሰቱ በነፃ የስልክ መስመር 7794 ወይም በአቅራቢያችሁ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ሪፖርት እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡
ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ
የሲዳማ ሕ/ጤ/ኢ/ ዳይሬክተር ጀነራል
ታህሳስ 30/2018 ዓም
ሀዋሳ፣ ሲዳማ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
- by admin
- on January 12, 2026
0