Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር በሲዳማ ክልል ርዕሰ ከተማ ሀዋሳ ተካሄደ።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ታህሳስ 03/2018

ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ በየነ በራሳን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባስተላለፉት መልዕክት የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመው በቅርቡ አቡዳቢ ላይ ፣ በተካሄደው አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡም ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ሲሉ ገልፀዋል።

የፖሊዮ በሽታ ለቤተሰብ፣ለማህበረሰብ ለሀገር ብሎም ለአለም ትልቅ ጫናን የሚፈጥር በሽታ በመሆኑ በ2017 በጀት አመት በሁለት ዙር የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በ10 ክልሎች 15 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዕድሜያቸው ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ መደረጉን ክብርት ሚኒስተሯ ጠቁመዋል።

በሀገራችን ፖሊዮን ጨምሮ ከ15 በላይ ክትባቶችን በመደበኛነት በመከተብ የማህበረሰባችን የጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እየሰራን ነው ሲሉ ዶ/ር መቅደስ ገልፀው ለአራተኛ ዙር በሚሰጠው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻም አንድም ህፃን ሳይከተብ እንዳይቀር ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሳ ጤና ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊና ምርታማነትን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ የቤተሰብ ብልፅግና ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግና ጤነኛ ትውልድ በመገንባት ክልላዊ ራዕይን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በክልሉ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ህፃናት ሳይከተቡ እንዳይቀሩ ሁሉም ሀላፊነቱን እንዲወጣ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ህብረተሰቡን ከተለያዩ የጤና አደጋዎች ለመከላከል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

ዶ/ር መሳይ አያይዘውም እንደ ሀገር ዋይልድ የሚባለውን የፖሊዮ አይነት ከሀገራችን ማጥፋት መቻላችን ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመው አሁንም አለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠውን የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለ24.5 ሚሊዮን ዕድሚያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረ በመሆኑ ቤተሰቦች፣ ማህበረሰቡ ህፃናትን የማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በመልዕክታቸው የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ ክትባት መሆኑን ጠቁመው ከዘመቻው ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ጉዳዮችን ገልፀዋል።

በዚህም ክትባት ያልጀመሩ ህፃናትን ማስጀመር፣ ክትባት ያቋረጡ ህፃናትን ማስቀጠል፣ ቆልማማ እግር ያላቸው ህፃናት ልየታ፣ ቤት ውስጥ ለረዥም ጊዜ በህመም የተኙ ዜጎችን መለየት እና በማርበርግ ቫይረስ በሽታ የተጠረጠሩና ምልክት የሚያሳዩ አካላትን ለይቶ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ ተቀናጅተው የሚሰሩ ተግባራት መሆናቸውን የቢሮ ሀላፊዋ አመላክተዋል።

ለሀገር ግንባታ ጤናማ ዜጋ ወሳኝ ነው ያሉት የሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው ገዳይ የሆነውን የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል በዘመቻ መልክ የሚሰጠው ክትባት እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በክልሉ የሚገኙ ወላጆች/አሳዳጊዎች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በክልላችን ክትባቱን የሚወስዱ ህፃናት አንድ ሚሊየን አርባ ዘጠኝ ያህል በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማት፣ የሚዲያ አካላት፣ባለድርሻ ተቋማት እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረሰቡ ዘመቻውን ስኬታማ ማድረግ እንዲችሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የአለም ጤና ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፍራንሲስ አሱሎ፣የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሀዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ክቡር አጋና ኔቶ፣የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ርመልካሙ አብቴ ቁልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎ክትባቱ ከዛሬ ታህሳስ 3 ጀምሮ እስከ 6/2018 ዓ.ም ድረስ ለአራት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል ተብሏል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ በየነ በራሳ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ እና የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣የሚዲያ ተቋማት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትሯና የዕለቱ እንግዶች በአዳሬ ሆስፒታል የተገነባውን ባለ 8 ፎቅ ህንፃ ፣የክልሉን ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት ዋና መ/ቤትና የክልሉ በላቦራቶር የስራ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት

ታህሳስ 03/2017 ዓ.ም

ሐዋሳ

ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

Web site: https://www.sphi.gov.et/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *