
የአፈጻጸም ግምገማው መድረክ ተሳታፊዎች ሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ፣ ሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት እና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ አጋር ድርጅቶች ሲሆኑ ፧ በክልሉ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረሰ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየዕለቱ የተተገበሩ ተግባራት ሪፖርት በሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዝርዝር ከቀረበ በኋላ ሰፊ ውይይት ተደርጓል ።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው እንደ ክልል በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው የበለጠ ውጤት ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
ዶ/ር መልካሙ አክለውም በየዕለቱ የጤና ባለሙያው ቤት ለቤት በመሄድ ትኩሳት ያለባቸውን /የታመሙ ሰዎች ፍለጋ (Active Case Search) እና ማህበረሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራትን በየደረጃው ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳሰበዋል ።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ዋና ዳይረክተር ዶ/ር ዳመነ ዳባልቄ ይህ ወረርሸኝ በክልሉ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ከሲዳማ ጤና ቢሮ ፣ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በርካታ የመከላከል ተግባራት እየተከናወኑ መቆየቱን አስታውቀው እንደክልል ወረርሽኙን የመከላከል ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ዳመነ ከዚህ በፊት የበሽታውን ቫይረስ ለመመርመር ናሙና ወደ ኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ላብራቶሪ እየተላከ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ግን በጤና ሚንስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ድጋፍ የመመርመሪያ ማሽን በመገኘቱ በክልላችን ውሰጥ መሥራት መጀመሩን ገልጸው በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ለወረርሽኙ መከላከያ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ኤሌክትሮኒክስ እና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በማበርከታቸው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩትን አመስግነዋል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት
ህዳር 22/2018 ዓ.ም
ሐዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/
































