Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የጤና ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለጤና ኤክስቴንሽኖችና ለጤና ባለሙያዎች በማርበርግ ቫይረስ በሽታ ላይ ስልጠና እየሰጠ ነው።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ህዳር 20/2018 ዓ.ም

የጤና ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በየደረጃው ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማርበርግ ቫይረስ በሽታ ላይ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ታውቋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በመልዕክታቸው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ መከሰቱ ከታወቀበትና በነበረው ቀጥተኛ ንክኪ በሀዋሳ ከተማም አንድ ሰው ለህልፈት መዳረጉን ተከትሎ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሀላፊው አያይዘውም ለህልፈት ከተዳረገው ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎችም አስቀድሞ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ተለይተው የምርመራና የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልፀዋል ።

የማርበርግ በሽታ በሀገራችን አዲስ የተከሰተ እንደመሆኑ ስርጭቱን ለመግታት እና ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለውን የጤና ባለሙያ በማሰልጠን በክልሉ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በጤና ሚኒስቴር ፣ በክልል ጤና ቢሮ እና በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ሀላፊው ተናግረዋል።

የማርበርግ ቫይረስ በሽታ የሚለይባቸው መሰረታዊ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶች፣ የመከላከያ መሳሪያዎች አጠቃቀም (PPE)፣ በሽታውን እንዴት በምርመራ መለየት እንደሚቻል፣ የለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት የሚደራጁበት መንገድ፣ የሕክምና አሰጣጥ ሂደት የስልጠናው አካል መሆኑ ተገልጿል።

ይህን ከፍተኛ ሥልጠና በግንባር ቀደምትነት የጤና ባለሙያዎች እንዲያገኙ ሲደረግ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከመከላከል ጀምሮ ማህበረሰቡ አስቀድሞ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲችሉ፣ ቫይረሱን በምርመራ ከመለየት ጀምሮ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ በመሆኑ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በመተግበርና ማህበረሰቡ እንዲተገብር በማድረግ የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ አቶ በላይነህ አሳስበዋል።

ማህበረሰቡም ራሱን ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ

20/03/ 2018 M.D

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

👇👇👇👇 ይመልከቱ

Website: https://www.shb.gov.et

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *