
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት 19/2018
የጤና ሚኒስቴር ለሲዳማ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር የሚውሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችንና አንቡላንሶችን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ርክብክብ አድርጓል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ድጋፉን በተረኩቡበት ወቅት እንደተናገሩት የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ከተማ መገኘቱ ከተረጋገጠበት ቀን ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እያደረጉ ያሉትን ፈጣን ምላሽና ቫይረሱን ለመቆጣጠር ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል ።
በዛሬው ዕለትም የወረርሽኝ ቁጥጥሩን ለማጠናከር የሚያግዙ አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጋቸው ርዕሰ መስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።
አቶ ደስታ አክለውም ጂንካ ከተማ ከህሙማን ጋር በነበረው ቀጥተኛ ንክኪ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆኑ ህይወቱ ካለፈው አንድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ጋር የተገናኙ ሌሎች ሰዎችን ለይቶ በመከታተልና ህክምና በማድረግ እንዲሁም የማህብረሰቡን ግንዛቤ ከፍ የማድረግ ተግባራት በየደረጃዉ በማጠናከር
ቫይረሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
እንደ ክልል የማርበርግ ቫይረስን የመከላከል፣ ቅኝት፣ ምላሽና ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመው ማህበረሰቡም ከጤና ሚኒስቴር የሚተላለፉ መረጃዎችንና የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመከታተልና በመተግበር የቫይረሱ መገለጫ የሆኑ መሰል ምልክቶችም ሲያስተውል በፍጥነት ለዚሁ አላማ ወደተዘጋጀው ህክምና መስጫ በመሄድ እንዲታከም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በጤና ሚኒስተር የሚኒስትሯ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ቫይረሱን በምርመራ ከመለየት ጀምሮ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል አቅም የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው የመከላከያ መንገዶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማህበረሰቡ እንዲተገብር በማስተማር የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቫይረሱ መገኘቱ ከተረጋገጠበት ጂንካ ከተማ በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችና ከተሞች የቅድመ መከላከል ተግባራትን አስቀድሞ በመስራት፣ ንኪኪ ያላቸዉን ሰዎች በመለየትና ክትትል በማድረግ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ተግባራትን በመምራትና ማስተባበር ባለሙያዎችን ከመመደብ ጀምሮ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አማካሪው በማጠቃለያቸው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከተገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት፣ እና የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ህበረሰቡ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን በመተግበርና ጥቆማዎችን በመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት
ህዳር 19/2017 ዓ.ም
ሐዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/
















