Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

ለህብረተሰብ የጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት ይገባል።

ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ

የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም

ለህብረተሰብ የጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት እንደሚገባ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት ለክልላችን ብሎም ለብሔራዊ ጤና ደህንነት” በሚል መሪ ቃል ባካሄደው አመታዊ ጉባኤ ላይ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ ከ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀምና ከቀጣይ አመት ዕቅድ በተጨማሪ በወባ በሽታ ላይ እየተካሄደ ያለ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥናት ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተደርጎበታል።

ውይይቱን የክልሉ ፕሬዝዳንት ማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ አማካሪ ክቡር አቶ ባጢሶ ዌዲሶ እና የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በጋራ የመሩት ሲሆን በዘርፉ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ለህብረተሰብ የጤና ስጋቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚያስችሉና ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት ላይ ያተኮሮ ሀሳቦች ተንፀባርቀዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒሴቲትዩት በበሽታ ቅኝትና ቁጥጥር እንዲሁም ምላሽ አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለው መሻሻል ይበል የሚያስብል እንደሆነ ክቡር አማካሪው ገልፀው ፤በክልሉ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማጠናከር በወባ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በሌሎች የጤና ችግሮች ላይ ከጤና ልማት አጋሮች፣ከዩኒቨርስቲዎች፣ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከግል የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ባህሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የተቋሙ ቁልፍ ተልዕኮ የህብረተሰብ ጤና አደጋና ስጋቶችን መቆጣጠር፣ ቅኝት ማድረግና ከተከሰቱም ፈጣን ምላሽ መስጠት በመሆኑ የጤና ተቋማት የርስበርስ መደጋገፍ በማጎልበት፣ በበጀት ዓመቱ የተለዩ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ብቃት ክፍተት በስልጠና በመሙላት የተሻለ ውጤት ማምጣት ተጠባቂ መሆኑን ዶ/ር ዳመነ በአፅንኦት ተናግረዋል።

በክልሉ ጫት በስፋት በሚያመርቱ አካባቢዎች ላይ በጫት ተክል ላይ በሚረጨው ኬሚካል ሳቢያ የሚመጣው ብክለት ትኩረት እንደተሰጠው በማመላከት ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት ሀሳብ አስተያየትም በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን በቀላሉ ለይቶ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል የአቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ ዘዴ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው በላብራቶሪ አገልግሎት ፣ በድንገተኛ ወረርሽኞች ቅኝት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ የመጣውን አመርቂ ለውጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል ።

በክልሉ የዘመነ መረጃ ዝግጅት፣አጠቃቀምና ሪፖርት ልውውጥ ሂደቱን በማጠናከር መረጃን ለተገቢው ውሳኔ የመጠቀም ባህሉ እያደገ መምጣቱን፣ ላቦራቶሪው በEID,HIV viral load, Genexpert እና TB culture አለም አቀፍ ስታንዳርድ ተከትሎ እየሰራ በመሆኑ ከኢትዮጵያ አክሬድተሽን አገልግሎት የአክሬድተሽን ምስክር ወረቀት መሸለሙም በዘርፉ የተመዘገበ ስኬት መሆኑን በመግለፅ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ጉድለቶችን ደግሞ በጋራ ርብርብ ማረም እንደሚገባ በአፅንኦት ተነስቷል።

በጉባኤው ማጠቃለያም የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ወረዳዎች 1ኛ ,በንሳ ወረዳ (ከምስራቃዊ ዞን)፣2ኛ, ወንዶ ገነት ወረዳ (ከሰሜናዊ ዞን) 3ኛ,ሁላ ወረዳ (ከደቡባዊ ዞን) ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የዕውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸው ጉባኤው ተጠናቋል።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ጥቅምት 13/2018ዓ/ም

ሀዋሳ

ተጨማሪ መረጃዎችን

“”””””””””””””””””””””””””””

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

Web site: https://www.sphi.gov.et/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *