
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥቅምት 17/2018 ዓ/ም
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት”የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት ለክልላችን ብሎም ለብሔራዊ ጤና ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2018 ዓ/ም ዕቅድ ላይ በመምከር ላይ ነው።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በመልዕክታቸው ሁሉን አቀፍ፣ ጥራቱን የጠበቀና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማፍጠን የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
ሀላፊዋ አክለውም የክልሉን ህብረተሰብ ከድንገተኛ አደጋዎች ለመጠበቅ በተከናወኑ የቅኝትና የአሰሳ ስራዎች በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ የመጣው አበረታች ለውጥ በየጊዜው የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግና የተጠናከረ የጤና ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ያላሰለሰ ጥረት እንደሆነ ጠቁመው፤ የተሻለ ጥራት ያላቸውን የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች በሁሉም የጤና ተቋማቶች ማስፋፋት፣ ማጠናከር እና ተደራሽ ማድረግ የዘርፉ ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም የቢሮ ሀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት በሚያደርሱ የጤና ችግሮች ላይ አግባብነት ያለው ጥናት በማድረግ በግኝቶቹ መነሻ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ አብራርተው የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታትና ከአየር ለውጡ ጋር ያለውን ተዛማጅነት በማጥናት ችግሩን ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ ክልላዊ መንግስት ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው ባለፈው በጀት አመት በኢኒስቲዩቱ ዋና ተልዕኮ ላይ በማተኮር የተከናወኑ የወረርሽኝ አሳሳና ቅኝት ስራዎች፣ ድንገተኛ ጤና አደጋዎችና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓቱ ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን አብራርተዋል።
በክልሉ የቅድመ ማስጠንቀቅ መልዕክቶችን በማስተላለፍ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልና ከተከሰቱ በኋላ ደግሞ ፈጥኖ በመቆጣጠር ህብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያጋጥም መሰራቱን ተናግረዋል።
በክልሉ በአራት ወረዳዎች ላይ የኩፍኝ ወረርሽኝ፣በአንድ ወረዳ ላይ m-pox ፣ኮሌራ እንዲሁም የወባ በሽታ ተከስቶ እንደነበር፣ ከተፈጥሮ አደጋም በአንድ ወረዳ ላይ የመሬት መንሸራተት አጋጥሞ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በየደረጃው በተደረገ ርብርብ የከፋ ውስብስብ ችግር ሳይከተል መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።
መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የላቦራቶሪ አገልግሎት ደረጃውን በማሻሻል፣ የድንገተኛ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓቱን ማዘመንና ማሳደግና እንደተቻለ ገልፀው ሙሉ በሙሉ ለማዳረስም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተጠቁመዋል።
በክልሉ የተጠናከረ የላቦራቶሪ አገልግሎት እንዲኖር በቅንጅት በተሰሩ ውጤታማ ስራዎች የጂን-ኤክስፐርት ማሽኖችን ቁጥር ከፍ በማድረግና አለም የደረሰበት ትልቁ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን የጂኖሚክስና ባዮኢንፎርማቲክስ ምርመራ ማስጀመር መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመው፤ አገልግሎቱን በማዘመን የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በምክክር ጉባኤው ላይ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀምን በመገምገም በ2018 ዓ.ም የነበረውን ጠንካራ ጎን በማጠናከርና በጉድለቶች ላይ ደግሞ በጋራ መክሮ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በሚያስችል መልኩ ሪፖርቶች ቀርበዋል።
በጉባኤው ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻን ጨምሮ፣ የክልሉ ፕሬዝደንት ማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች አማካሪ ክቡር አቶ ባጢሶ ዌዲሶ፣ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት አየለች ሌዳሞን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮና የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የማኔጅመንት አባላት፣ የዞን ጤናና ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የስራ ሀላፊዎችና እንዲሁም አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ጥቅምት 13/2018ዓ/ም
ሀዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን
“”””””””””””””””””””””””””””
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/




























