Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የማህበረሰባችንን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሻሻል የዲጂታል ሚዲያ ሚና የጎላ ነው። አቶ በላይነህ በቀለ

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በወቅታዊ እስትራቴጂያዊ ጉዳዮች በተለይም የወባ ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ስራ እና በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ላይ ዲጂታል ሰራዊቱን ለማንቃት የሚያግዝ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በመልዕክታቸው በጤናው ዘርፍ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማረጋገጥ ፤ የማህበረሰባችንን በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል የዲጂታል ሚዲያ ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተግባራትን በተጀመረው የሚዲያ ንቅናቄ በማጀብና በማነቃነቅ የወባ በሽታ በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስና ብሎም ወባን ጨርሶ ለማስወገድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባም ም/ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

አቶ በላይነህ አያይዘውም የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ገቢያቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ አስቀድመው በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ ያልተገባ የጤና ወጪ ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተው በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል ።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዶጊሶ በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ጨምሮ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል ተገማች ያልሆኑ የጤና ተግዳሮቶችን ለመመከት እና በጤናው ዘርፍ ለሚጠበቁ ለውጦችን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ የሚዲያ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦችና ውጤቶች ቀጣይነት መረጋገጥ እንደሚገባው አውስተው ይህንንም ዕውን ለማድረግ ወቅታዊ መረጃዎችን ማድረስና በየደረጃው ዲጅታል ሰራዊቱን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ዳይሬክተሩ አክለውም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አጠቃቀምን ከማሻሻል አንፃር የዲጂታል ሰራዊቱን በተገቢው በመጠቀም ስራው የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዲያመጣ መረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።

የዲጂታል ሰራዊት ግንባታውን በማሳለጥ ከማህበረሰብ ጤና አጠባበቅና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና ስርዓት በመፍጠር ማገልገልና በሴክተሩ የታቀዱ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ፣የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ፋይዳ ፣የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የጤና ተግባቦት ፎካሎች እና የሚዲያ ተቋማት ሚና የሚሉ ርዕሶች ላይ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በቀጣይም የዲጂታል ሚዲያ ሰራዊቱን የሚያጠናክሩ መሰል ምክክሮች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመው አማራጭ ሚዲያዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋት፣ አመራሩ አጀንዳውን አጠንክሮ እንዲይዘው ማድረግ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማሻሻልና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል ።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት፣ የክልሉ ባለድርሻ ሴክተር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒዩኬሽን የስራ ኃላፊዎች ፣የክልሉ ተጠሪ ተቋማት የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ፣ የዞን ጤና ዩኒትና የወረዳ ጤና ፅ/ቤት ሀላፊዎችና የጤና ተግባቦት ፎካሎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የሲዳማ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

👇👇👇👇 ይመልከቱ

Website: https://www.shb.gov.et

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *