
Ethiopia Launches the First Regional Action Plan for Health Security
——————————
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የክልላዊ የጤና ደህንነት የዕቅድ አቅም ግንባታ ማስጀመሪያ አውደ ጥናት በሲዳማ ክልል በይርጋለም ከተማ ከነሀሴ 26 – 28/2017 ዓ.ም ተካሄደ። ይህ የክልላዊ የጤና ደህንነት ዕቅድና ትግበራ በአቅም ግንባታ ሂደት ውስጥ የስርዓት አስተሳሰብን እንደሚያሳድግ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ዕቅዱ ከአለምአቀፍ እና ከሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻሉ ተሞክሮዎችን እንዳግብአት ተጠቅሟል።
የክልላዊው የጤና ደህንነት ዕቅድ፣ በክልል እና ከክልል ውጪ ያሉ የህብረተስብ ጤና ድንገተኛ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመለየት እና ምላሽ ለመስጠት ያለውን የጤና ደህንነት አቅም በማጠናከር ላይ የሚያተኩር ሲሆን ይህ ደግሞ በክልላዊ የጤና ደህንነት አቅም ምዘና ወቅት የታዩ ክፍተቶችንና ችግሮችን በማጥበብ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ የሲዳማ ክልል የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የክልሉ የጤና ደህንነት ዕቅድና ትግበራ ውጤታማ እንዲሆን የአመራሩን ቁርጠኝነት አሰታውቀው ክልሉ ለክልላዊ እና ለሀገራዊ የጤና ደህንነት ስትራቴጂዎች እንዲሁም ለአለምአቀፍ የጤና ደንብ እና ለ“አንድ ጤና” አተገባበር በሁሉም የሲዳማ ክልል ላይ ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
አቶ ኡጋሞ አናጋ፣ የሲዳማ ክልል የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ውጤታማ የክልላዊና ሀገራዊ አቅም እንዲኖር ካስፈለገ የክልል የጤና ደህንነት አቅምን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጤና ስጋቶች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውን ያሳየ በመሆኑ ለህብረተስብ ጤና ደህንነት የጋራ አካሄድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የሲዳማ ክልል የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተስብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በድሉ በዲጎ፣ በበኩላቸው የጤና ደህንነት ዕቅድን በማሳደግ ረገድ የትብብርና የጋራ አካሄዶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል። ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል ከአለምአቀፍ የጤና ደንብ ቴክኒካል ደረጃዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ በክልላዊ የጤና ደህንነት አቅም የጋራ ምዘና መሰረት የተደረገውን የሲዳማ ክልል የጤና ደህንነት አቅም ምዘና ውጤት ጠቅሰው አውደ ጥናቱ ባለብዙ ዘርፍ ትብብርን ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም በአጽንዖት ገልጸዋል።
ይህ አውደ ጥናት በቀጣይ በቀሪዎቹ 13 ክልሎች ለሚካሄዱ ተመሳሳይ ትግበራዎች እንደ ምሳሌነት እንደሚያገለግልም ለማወቅ ተችላል። አውደ ጥናቱ፣ በሲዳማ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የሕ ብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት አለም አቀፍ የጤና ደንብ እና አንድ ጤና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን፣ የተሳካ እንዲሆን ከፌዴራል የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ አጋሮች እንዲሁም ሪዞልቭ ቱ ሴቨ ላይቨ በቴክኒክ እና በፋይናንሰ እገዛ አድርገዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ አለምአቀፍ የጤና ደንብ የጤና ደህንነት አቅሞችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን በማጠናከር የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል፣ በመለየት እና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ውጤታማ የሆኑ ሰራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነሐሴ 29/2017 ዓ/ም
ሀዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎች የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/
























































