
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና የጤና ተግባቦት ስራዎችን ማጠናከር ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ ከዞንና ከወረዳ የጤና ትምህርት ባለሙያዎች ጋር አካሂዷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ በላይነህ በቀለ በመልዕክታቸው የማህበረሰቡን የበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስና ጤናማና አምራች ዜጋ የመፍጠር ራዕይን እውን ለማድረግ የማህበራዊ ባህሪ ለውጥ ተግባቦት /SBCC/ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሀላፊው አያይዘውም ከክልል ጀምሮ ያለውን የጤና ተግባቦት ስራን እስከ ወረዳ አጠናክሮ በማስቀጠል በሽታን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻልና የህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸው አሳስበው ለዚህም የጤና ኮሚዩኒኬሽን ፎካሎች በህዝቡ አእምሮ ውስጥ የሚያሰርጹት የተግባቦትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስትራቴጂክ ኮምዩኒኬሽን እሳቤ የተቃኙ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦችና ውጤቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የተግባቦትና የሚዲያ አካላት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለፁት የቢሮው የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዶጊሶ በበኩላቸው በሴክተሩ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉ ወቅታዊ መረጃዎችን ለማድረስና በየደረጃው የዲጅታል ሰራዊቱን ለማጠናከር ከዞንና ከወረዳ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያዎች ጋር መምከር ማስፈለጉን ጠቁመው በተሻለ መልኩ የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን እንቅስቃሴን በማጠናከር በዘርፉ የጠነከረና ቀጣይነት ያለው የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማስቻል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ወቅቱ የዲጂታል ሚዲያ ዘመን እንደመሆኑ የዲጂታል ሰራዊት ግንባታውን በማሳለጥ ከማህበረሰብ ጤና አጠባበቅና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና ስርዓት በመፍጠር ማገልገልና በሴክተሩ የታቀዱ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የቢሮው በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቃሬሳ ዳፋርሳ በበኩላቸው በየደረጃው የጤና ተግባቦት ስራውን በማጠናከር ፣ ወቅቱን የጠበቀና ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ መረጃን ከትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በመውሰድ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማጠናከር በህዝቡ ውስጥ የሚስተዋለውን የተሳሳተ አመለካከትና የተዛቡ መረጃዎችን ፈጥኖ ማረም እንደሚገባ ጠቁመው ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን መጠቀምና የዲጂታል ሰራዊት ግንባታውን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በመጨረሻም በህ/ግንኙነት ፣የጤና ተግባቦት እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የቀረቡ ሰነዶችን መሰረት ያደረገ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ በህ/ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ የስራ አቅጣጫ በመስጠት የንቅናቄ መድረኩ ተጠናቋል ፡፡
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች



ይመልከቱ
Website: https://www.shb.gov.et
















