Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የጤናውን ዘርፍ ግቦች ለማሳካት የጤና ባለሙያዎች ሚና የላቀ ነው። ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሲዳማ ክልል “የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር እድገት!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ክልላዊ የጤና ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለፁት ሲዳማ ክልል ከሆነ ጀምሮ ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ በመሠረተ-ልማት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበረሰብ አቅም ግንባታ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በተደረገው ጥረት ባለፉት አምስት አመታት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የተቀረፁ ልዩ ልዩ የጤና ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ በማፍራት የተከናወኑ ተግባራት በእጅጉ አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህ ስኬት የተገኘው በጤና ባለሙያዎች እና በዘርፉ ተዋናዮች መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የጤና ባለሙያዎችን የመብት ጥያቄ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ያዳመጣቸው መሆኑን ገልፀው ነገር ግን ጥያቄዎችን ለሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መጠቀም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
በቀጣይም የክልሉ መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው ርዕሰ-መስተዳድሩ የገለፁት።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የጤናውን ዘርፍ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን ያነሱ ሲሆን፤ በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች 4 አዳዲስ ሆስፒታሎች፤ 8 አዳዲስ የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች የተገነቡ እና ከ 224 በላይ የጤና ኬላዎች እድሳት የተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ተቋማቱ በሰው ሀይልና በግብዓት በማሟላት ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ባለፉት ሳምንታት በየደረጃው ካሉ የጤና ባለሙያዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ሪፖርት የሚቀርብ ሲሆን፤ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፤ የጤና ተቋማት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
👇👇👇👇 ይመልከቱ
Website: https://www.shb.gov.et

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *