Skip to content 
በወባ በሽታ ምርምር ዙሪያ የምርምር እቅድ ነድፈው ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር አብረው ሲሰሩ የነበሩትን የምርምር ስራዎች ለመገምገም ከሶስት የአሜሪካ ዩንቬርሲቲዎች (University of North Carolina, Brown University እና Notre Dame University) የተውጣጡ ስድስት ከፍተኛ የምርምር ልኡካን ቡድን ከኢንቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ከኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ብሎም ለማጥፋት የሚደረገው የምርምር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በዩንቬርሲቲዎቹና በኢንስቲትዩቱ መካከል በትብብር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ዉጤታማና አበረታች መሆኑን ጠቁመዉ በጋራ መሥራቱና የትብብር ስራው ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዉ ለስኬቱም ኢንስቲትዩቱ የሚጠበቅበትን ድጋፊ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ የምርምር ልኡካን በበኩላቸዉ ወደ ኢንስቲትዩቱ እንዲመጡ ያደረጋቸው ትልቁ ጉዳይ ኢንስቲትዩቱ በወባ ምርምር ዙሪያ እያካሄደ ያለዉ ስራ አበረታች በመሆኑ የምርምር ስራዎቹን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አድማሱንም ለማስፋት፣ በአየር ንብረት ለዉጥና በሽታ ኢፒደሚዮሎጂ ላይ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በወባ ምርምር ዙሪያ ውይይት ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ የተለያዩ የሳይንስ ምሁራንና የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች በተገኙበት ከዩንቬርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ካሮላይና፣ ብራዎን እና ኖተር ዳም ዩንቬርሲቲዎች ጋር በመተባበር ወባን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሳይንሳዊ ሴሚናር ሚያዚያ 22/2017 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል ከቀኑ 7፡30 እስከ 11፡30 ድረስ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የሴሚናሩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በምርምር ዘርፉ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ምርምሮች ማቅረባቸዉ ፋይደዉ እጅግ የላቀ መሆኑን ጠቁመው፤ ወቅቱ ወባን ለመቆጣጠር መንግስትና ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በጋራ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንከታተል የሚያደርግ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ገረመዉ ጣሰዉ የኢንስቲትዩቱ የወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይርክቶሬት ዳይሬክተር የኢንቲትዩቱ ታሪካዊ አመሰራረት፣የኢንስቲትዩቱ አሁናዊ አደረጃጀትና በወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይርክቶሬት ሥር በወባና በወባ ትንኝ ቁጥጥርና መከላከል ዙሪያ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ሳይንሳዊ ጽሑፍ በዝርዝር አቅርበዋል።
በተጨማሪም ላለፈዉ አንድ ዓመት ከEpidemiology and Determinants of Emerging Artimisnin-resistant Malaria in Ethiopia (MAREE) ፕሮጀክት ስራ የተገኘውን የምርምር ዉጤት በፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በዶ/ር አሸናፊ አሰፋ የቀረበ ሲሆን ከአሜሪካ በመጡ ሳይንቲስቶች የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን እና (Sequencing, Pfhrp2/3 assay and Invitro culture) የወባ ስርጭትና ብግርነት በተመለከተ ያለውን ወቅታዊ እውቀት አስመልክቶ በመረጃ የተደገፈ ምክረ ሃሳብ አጋርተዋል፡፡
በሳይንሳዊ ጉባኤው ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ መጨመር ምክንያቶችን አስመልክቶ የተካሄደውን የመጀመሪያ ደረጃ የጥናት ውጤት የቀረበ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ጊዜውን ባአማከለ መልኩ ያበለጸገውን የወባ ጥናት አቅም መጠቀሙን አስታውቋል፡፡
- by admin
- on September 17, 2025
0