Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

ኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ

——————

ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የክልል ላቦራቶሪዎችን የሚሰጡትን የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ግምታቸው 158 ሚሊየን ብር የሚጠጉ የተለያዩ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ።

የድጋፉ ዋና ዓላማው የሕብረተሰብ የጤና ችግር የሆኑት ተህዋሲያን የመለየት አቅምን ማሳደግ፣ የመረጃ ቅብብሎሽን ማዘመን፣ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደራሽ ላልሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ የትሪፕል ፓኬጆች ድጋፍ ነው፡፡

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይም የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንደገለጹት የላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎትን ለማጠናከር የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፣ የላቀ ደረጃ ያላቸውን የላቦራቶሪ ምርመራ ከማጠናከር አንጻር በኢንስትቲዩት ውስጥ የላቦራቶሪ ጥራት ቁጥጥር ናሙና ማምረቻ እና የባዮባንክ ማዕከል እየተገነባ እንደሚገኝ እና በቀጣይም የቢኤስ ኤል 3 (BSL 3) ሪፈራንስ ላቦራቶሪ ለመገንባት ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በክልል ደረጃም ከሃያ ሳምንት በላይ የቢኤስ ኤል 2 (BS-2) ሪጅናል ላቦራቶሪዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዉ ኢንስቲትዩቱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የላቦራቶሪ የጥራት ፍተሻ ስርዓት ሶፍትዌር (EQA database system software) ያበለጸገ መሆኑን፣ ይህንን ሶፍተዌር በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ስራ ለማስገባት ለክልል ጥራት ፍተሻ ማዕከላት (EQA Centers) የአይቲ (IT) መሳሪያዎችን በዛሬው ቀን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዘመኑ የሚጠይቃቸውን የላቦራቶሪ የምርመራ መሳሪያዎችን በማሟላት ሕብረተሰቡን በሪፈራል ስርአት አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱ ለማዳረስ ይቻል ዘንድ የክልል ላቦራቶሪዎችን አቅም በመገንባት እና በማደራጅት ለሕብረተሰቡ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን በቅርበት እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የተደረገው ድጋፍ ይህንን በተሻለ ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ሳሮ አብደላ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የላቦራቶሪ አገልግሎትን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ሰራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸው፤ ለክልል ጥራት ፍተሻ ማዕከላት ማጠናከሪያ የሚሆኑ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮችና የማይቋርጡ የኃይል አቅርቦቶችን (UPS) በርክክብ ስነ-ስርዓት ወቅት ለክልሎች የተከፋፈለ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ተደራሽ ላልሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች የላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ አማራጭ የላቦራቶሪ ናሙና ሪፈራል ሲስተም ተዘርግቶ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ዛሬ የተደረገው የትሪፕል ፓኬጅ ድጋፍ አገልግሎቱን በማጠናከር ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የላቦራቶሪ የምርመራ ተደራሽነትን የሚያግዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በርክክብ ስነስርዓቱ ወቅት ግምታቸው 1,237,625 USD (158,416,000 ብር) የሆኑ መሳሪያዎችን ለክልሎች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የተደረገውን ድጋፍ ክልሎች ለታሰበው ዓላማ በማዋል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀደውን ዲጅታላይዝድ የጥራት ፍተሻ ሂደት የማረጋገጥ ኃላፊነትን በመውሰድ የበኩላቸውን ጉልህ ሚና እንዲወጡ ከመድረኩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

www.ephi.gov.et/news

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *