Skip to content 
በመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የበይነ መረብ ስብሰባ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባስተላለፉት ጥልቅ መልዕከት ተጀምሯል።
ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው በመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት ዙሪያ በወጡ አዳዲስ ህጎች ፣መመሪያዎችና የአሠራር ለውጦች ላይ ሀገራዊ ውይይት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ የህዝብን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላትና በመድሀኒት አቅርቦት ላይ ያለውን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የተሻሻለና ወጥ የሆነ የአሰራር ሂደት መከተልና የመድሀኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ይበልጥ ማዘመን አስፈላጊ በመሆኑ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በ2016 ዓ/ም በኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት አስፈላጊ መድሀኒቶችን ከማግኘት አንፃር እንደክፍተት የተለዩ ችግሮችን በ2017 በጀት አመት አጋማሽ በማሻሻል በተለይም መሰረታዊ መድሀኒትን 78 በመቶ በማድረስ
የማህበረሰቡን የመድሀኒት ፍላጎት ለሟሟላት የሚደረጉ ርብርቦች በየደረጃው ተጠናክረው እንደቀጠሉም ነው የተገለፀው።
ከዚህ ቀደም በጤና ዘርፍ ለተመዘገበው አመርቂ ውጤትም ሆነ እየተተገበረ ባለው የኢንቨስትመንት ልማት ዕቅድ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ማሻሻል ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ በተለያዩ ጊዜያት በተሻሻሉ ስትራቴጂዎችና አሰራሮች በመመራት የመድሀኒት አቅርቦቱን 90 በመቶ ከፍ በማድረግ ተደራሽነትን ከጥራት አማክሎ ለመፈፀም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሠሩ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል ።
ህብረተሰቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተገቢው ለመመለስ ቅንጅታዊ አሰራርን ማሻሻል እና የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አቅርቦት ማጠናከርና አለማቀፋዊ ስታንዳርዱን ያሟሉ ማድረግ ለመድኃኒት አቅርቦት ችግር የመፍትሄ ሀሳብ ተደርገው የተለዩ መሆኑን ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው ከዳሰሷቸው ሀሳቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዙሪያ በወጡ አዳዲስ ህጎች ፣መመሪያዎችና የአሠራር ለውጦች ዙሪያ ሰነድ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መድኅኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ማጎልበት የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አመላክተው ይህንንም መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ፣አዳዲስ ህጎችን መተግበር ፣የአቅርቦት ስርዓቱን ማሻሻል ፣የግዢ ስርሃቱን ማጠናከር የማህበረሰብ ፍርማሲዎችን ማሻሻል፣በየደረጃው ተጠያቂነት ያማከለ ተግባራትን መፈፀም ተጠባቂ መሆናቸውን አስገንዝበዋል ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዙሪያ እየተደረገ ባለው የበይነ መረብ ውይይት ላይ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት አባላት፣ የጤና ቢሮ ተጠሪ ተቋም አመራሮች፣ በኢፌዲሪ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ንማኔ ፣ የሁሉም ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎችና የሎጅስቲክ ስራ ሂደት አስተባባሪዎች ፣ የሁሉም ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የሎጂስቲክ የስራ ሂደት አስተባባሪዎች፣ የሁሉም ሆስፒታል ስራ አስኪያጆችና የመድኃኒት ክፍል ኃላፊዎች ፣ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ወረዳ ለስብሰባው የተመረጡ ጤና አ/ጣቢያ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ
መጋቢት 3/2017 ዓ.ም