Skip to content 
ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግቦች ደህንነታቸዉና ጥራታቸዉ የተረጋገጠ እንዲሆኑ ለማድረግ የቁጥጥር ስርሃቱን ማጠናከር እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ መገለፁ ታውቋል ፡፡
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ በመልዕክታቸው ምግብ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ጤና ፣አካላዊና አህምሮአዊ ዕድገነት ጠቃሚ መሆኑን በማውሳት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግቦች ደህንነታቸዉና ጥራታቸዉ የተረጋገጠ መሆን ይጠበቅበታል ፤ለዚህም ህብረተሰቡን የቁጥጥር ስራው ባለቤት ማድረግ አማራጭ የሌለው ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ገልፀዋል ።
ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀሉ የተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች መበራከት፣ ከደረጃ በታች የሆኑ የምግብ ምርቶች ፣በተለይም በጤፍ ና ፣ በበርበሬ ግብይቶች ላይ ይበልጥ እንደሚስተዋል በአብነት አንስተዋል ።
ይህንንም መነሻ በማድረግ ባለስልጣኑ የችግሩን አሳሳቢነት ሲገልፁ በዚህ ወር ብቻ 7 ናሙናዎች ወደ ዋናው መስሪያ ቤት በመላክ 5 ቱ ለጤና ጎጂ የሆኑ አፍላ ቶክሲኖችን መያዛቸውን አረጋግጠናል በማለት እነዚህ ምርቶች በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከሉት ውስብስብ የጤና ችግሮች ቀላል አለመሆናቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባን አስረጂዎች ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፋታት የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ፣ህብረተሰብ መሰል ህገወጥ ተግባራት ሲያጋጥሙት ጥቆማ በመስጠት የቁጥጥሩ አካል በመሆን ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርዳቸው አናቶ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ ጤናና ጤና ነክ ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የቁጥጥር ስርአቱን ለማጠናከር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል ይሁን እንጂ ከተሜነት መስፋፋት ጨምሮ የህገ ወጥ ንግድ መበራከት በተለይም የጤና ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ሳይኖር የንግድ ፈቃድ ሳይሟላ የንግድ ተግባራትን መፈፀም፣የአወጋገድ ስርሃቱ ችግር ያለበት መሆኑ በተግዳሮትነት እንደሚገለጽ አመላክተዋል፡፡
የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳታፊ በሆኑበት በውይይት መድረክ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤናና ጤና ነክ ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን 2017 ዓ.ም ግማሽ አመት አፈፃጸም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
ውይይቱን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘውዲቱ ገ/መስቀል ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ ፣የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርዳቸው አናቶ በጋራ መርተውታል ።
ተሳታፊዎች በተሰጡ አስተያየት ሕብረተሰቡ የሚጠቀምባቸዉ ምግቦች ደህንነታቸዉና የተረጋገጠ እንዲሆን አቀናጅቶ በመስራት ጤና ላይ የሚደርሰዉን ተፅዕኖ መቀልበስ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በማውሳት የጤናና ጤና ነክ ተቋማት የቁጥጥርን በማጠናከር ጥራታቸው የተጠበቀ ምግብና የምግብ ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መሰራት እንደሚገባ አመላክተዋል ።
በመጨረሻም በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣የክልሉና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤናና ጤና ነክ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሣታፊዎች መሆናቸው ታውቋል።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ