Skip to content 
የሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት የካቲት 21/2018 ዓ.ም
በሲዳማ ክልል የማርበርበርግ ቫይረስ ስርጭትን በመከላከል ሂደት የላቀ ሚና ለተወጡ አካላት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የፌደራልና የክልሉ ቁልፍ አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተከናውኗል።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ በመልዕክታቸው በሀገራችን ጅንካ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ ከተሰራጨ እንደ ሀገር ብሎም በክልላችን በርካታ ወገኖቻችንን ሊያሳጣን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ያጫረ፣ ያለንን ውስጣዊ ጥንካሬ እንድንፈትሽ ደግሞ እድል የፈጠረ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
እንደሀገር ብሎም በክልሉ በተሰጋው መጠን ጉዳት ሳይከሰት በሽታውን መቆጣጠር መቻሉ የመጀመሪያው የፈጣሪ እገዛ ነው ሲሉ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀው ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የታየው የአመራር ክህሎት ሌላኛው ጥንካሬ መሆኑን ተናግረዋል ።
ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ልምዳችንን ተግባራዊ በማድረግ፣ በተቀናጀ የጤና ስርዓትና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ፣በጤና ባለሙያዎቻችን ግንባር ቀደም ተሰላፊነት በሽታውን መቆጣጠር ተችሏል፤ ለዚህም ምስጋናና እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው ሲሉ አቶ ደስታ አክለው ገልፀዋል ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ማጥፋት መቻሉ የጤና ስርዓቱ ላይ የተጣለውን ጠንካራ መሰረት ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ሲዳማ ክልል ህዝቡን አስከፊ ከሆነው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ለመጠበቅ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ የክልሉ ቁልፍ አመራሮች፣በየደረጃው ያሉ የጤናው ሴክተር የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚዲያዎች አጠቃላይ ማህበረሰቡ የሰጡት ፈጣንና የተናበበ ምላሽ የሚደነቅ ነው ሲሉ ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ክብረ-በዓላት ላይ ጭምር ጥንቃቄ የተሞላ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ የተሰራው ስራ ቫይረሱ ባለበት እንዲቆም ጉልህ ፋይዳ እንደነበረውም ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለው ገልፀዋል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ለመቆጣጠር የሚያስፈልገውን የቴክኒክ አቅም እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳላት ያረጋገጠ መሆኑን ገልፀው በቫይረሱ ህይወታቸውን ላጡ የጤና ባለሙያና ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር ያደረገችው ስኬታማ ጥረትና አመርቂ ውጤት በጠንካራ አመራር፣ በባለሙያው ቁርጠኝነት፣በፈጣን ምላሽ እና በተቀናጀና በተናበበ ፈጣን የላቦራቶሪ ምላሽ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደሀገር የተመዘገበው ውጤት የጤና ፖሊሲውን ጥንካሬ፣ የጤና ባለሙያዎችን እና ባለድርሻ አካላት የጋራ የመተባበር እና የመተጋገዝ ውጤት መሆኑን ገልፀው ለዚህም የጤና ተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ስራ ትልቅ ሚና እንደነበረውም አስታውሰዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ እንደሀገር በተቀናጀ እና በጠንካራ የበሽታ መከላከል ስልት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን መቆጣጠር መቻሉን ጠቁመው የፈጣሪ እርዳታ ታክሎበት በጋራ ጥረትና ርብርብ ከሰራን የማንወጣው ችግር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በክልሉ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የተዘጋጀው ፕሮግራም የአገር ባለውለታ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን፣ አመራሮችን፣አጋሮችንና ባለድርሻ አካላትን ለማመስገን ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፌደራል ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አካላትና ባለሙያዎች ከየመዋቅሩ የተሳተፉ የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች፣ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ቫይረሱን ለመከላከል ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
የካቲት 21/2017 ዓ/ም
ሀዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎች የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

































































