
———————–
የኢትዮጵያ የሕብረተሰበ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል፣ ከካሊፎርኒያ ዴቪስና ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በጌትስ ፋውንዴሽን ድጋፍ፣ በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨው (DFS-IoFA) ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት በይፋ አስጀምረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የነርቭ ዘንግ ክፍተት (Neural Tube Defects /NTDs/) ችግርን በዘላቂነት ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን በአዮዲን እና ፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨውን የጥናት ውጤት ይፋ ለማድረግ እና ወደፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሰራጨት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ጥር 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተሰብስበዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ እናቶችን እና ሕፃናትን ልንከላከላቸው ከምንችላቸውና በወሊድ ጊዜ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ አካል ጉዳቶች ለመጠበቅ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ታሪካዊ እርምጃ የተወሰደበት መሆኑንና በአዮዲን እና ፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨውን በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ቤተሰቦችን መጠበቅ፣ ማህበረሰብን ማጠናከርና ለእያንዳንዱ ሕፃን ጤናማ የሕይወት ጅማሮን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መልካሙ አለበል በዚህ ሀገራዊ የስነ ምግብ አጀንዳ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ እንደነበርና የሁሉም የባለድርሻ አካላት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ለዚህ ፕሮግራም እውን መሆን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ ይህ በአዮዲን እና ፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨው ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ መሆኑን በሳይንሳዊ ምርምር ተረጋግጧል፤ ኢትዮጵያ የአዮዲን እጥረት ችግርን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ጨውን በአዮዲን እና ፎሊክ አሲድ (DFS-IoFA) ማበልፀግ መጀመሯ የእናቶችንና የሕፃናትን ጤና ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት ቀጣይ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው ኢንስቲትዩቱ ጥልቅ ሳይንሳዊ ምርምርን፣ የኢንዱስትሪ ሙከራዎችን እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን በመጠቀም የማበልፀግ ሂደቱ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ውጤታማ እና በሀገር ውስጥ አቅም የሚከናወን መሆኑን አረጋግጧል በማለት ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው ይህ እርምጃ ከብሔራዊ የምግብ እና የሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲ፣ ከሰቆጣ ቃል-ኪዳን እና ከተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን በሥርዓተ-ምግብ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሀገር እንድትሆን ያደርጋታል በማለት አስረድተው በዚህ ችግር ፈቺ ምርምር ላይ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል።
ከመድረኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛው የነርቭ ዘንግ ክፍተት (NTD) ጫና ያለባት ሀገር ስትሆን፣ ከየ10,000 ውልደቶች ውስጥ በ80ዎቹ ላይ ችግሩ ይስተዋላል፤ ይህም ከአህጉሪቱ አማካይ ጋር ሲነጻጸር በሶስት እጥፍ ይበልጣል። ይህ ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው እናቶች ከመፀነሳቸው በፊት እና በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ 28 ቀናት ውስጥ በቂ የፎሌት (Folate) ንጥረ ነገር ባለማግኘታቸው ነው።
የአጋር ድርጅቶች እና የባለድርሻ አካላት ኃላፊዎችም በዚሁ መድረክ ላይ የየበኩላቸውን መልዕክቶች አስተላልፈዋል።
www.ephi.gov.et/news











