
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ የመንስኤዎች መጠንን የሚያሳይ አገር አቀፍ የጥናት ውጤት ጥር 15/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይፋ አደረገ፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ ለጤና ሚኒስቴር፤ ለክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት የጥናቱን ውጤት ይፋ በማድረግ ለፖሊሲ አውጭዎች እና ውሳኔ ሰጭ አካላት ለፖሊሲ ውሳኔ አና ለፕሮግራም አቅድ እንደ መነሻ እንዲያገለግል እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች ተጠናክረው ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር የፕሮግራሙ መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአሁን ጊዜ እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና ችግር መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን በጥናቱ የተገኙ ለተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ የመንስኤዎች መጠን እንደ ጤና ሚኒስቴር ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆኑን፣ በተለይም ችግሩን በተሻለ ሁኔታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ የጥናቱን ተግባራዊነት በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ሁሉ ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር በቀጣይ በሚደረጉ ማንኛውም የጤና ስራዎች ሁሉ ጥናቱን መሰረት ያደረጉ እንደሚሆኑ፣ በተለይም ማንኛውም ሰው ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት አጋላጭ መንስኤዎችን የመከላከሉን ስራ ትኩረትና ኃላፊነት በመውሰድ እራሱን ከእነዚህ ችግሮች ሊጠብቅ እንደሚገባ ሚኒስትሯ አያይዘው አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ጥናቱን
አስመልክቶ እንደ ተናገሩት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተሻለ መንገድ ለመከላከል ለመቆጣጠር ያመች ዘንድ የተካሄደው አገር አቀፍ ጥናት ፖሊሲያዊ እና ውሳኔያዊ ተግባራትን ለማከናወን በርካታ መረጃዎች የተገኙበት በመሆኑ ጤና ሚኒስቴር ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ላለው የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት ትልቅ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የጥናቱ ውጤት በርካታ ጠቃሚና ወሳኝ ጉዳዮችን በመረጃነት ያቀረበ መሆኑን ከመጠቆማቸውም በላይ በጥናቱ የተሳተፉትን ከፍተኛ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን እንዲሁም የፋይናንስ እና አስፈላጊ በሆኑ የቴክኒክ ድጋፍ ላደረጉ አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የተለያዩ የአጋር አካላት ኃላፊዎችና ተወካዮች ጥናቱን አስመልክቶ መልክታቸውን ያስተላላፉ ሲሆን አቶ ግሩም ታዬ የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪና የጥናቱ አስተባባሪ አጠቃላይ የጥናቱን ዓላማዎች፤ የጥናቱን ዘዴዎች፤ሂደቶችን እናውጤቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው የጥናቱ ውጤቶች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ዶ/ር አደራጀው መኮንን እና አቶ ግሩም ታዬ ከጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ህይወት ሰለሞን እንዲሁም ከአለም ጤና ድርጅት ዶ/ር አስማማው በዛብህ ማብራሪያና ምላሽ ከሰጡ በኋላ አውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡
የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች፣ እና የአጋር አካላት ኃላፊዎች እንዲሁም ተወካዮች ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ተሳትፈዋል፡፡
www.ephi.gov.et/news















