Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአበረታች ቅመም/ዶፒንግ ምርመራ በሀገር ውስጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ::

—————————

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በሀገር ውስጥ የአበረታች ቅመም ወይም ዶፒንግ ምርመራ ማድረግ የሚያስችለውን የአትሌቶች ባዮሎጂካል ፓስፖርት ላቦራቶሪ ለማቋቋም ዛሬ ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ። ላቦራቶሪው በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ አስከ 2500 ናሙናዎች የመቀበል አቅም ይኖረዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን የጤና ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ እንደነበረና እየሰራም እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህንን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠቀበ የላቦራቶሪ ግንባታና ትግበራም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየዘመነ በመጣው በኢንስቲትዩቱ አቅም ሊሰራ መሆኑ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ እያመጣ ያለው ስኬት አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል።

የ ኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ ተቋማቸው ላለፉት ከሰባት ዓመታት በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰራ የነበረ ሲሆን በየሶስት ዓመቱም የብቃት ፍተሻ እንደሚደረግለት እናም ለዚህ ታላቅ ስኬት ለሆነው ላቦራቶሪ እውን መሆንም ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ ሲሰራ እንደነበር ገልጸው ላቦራቶሪው ለሌሎች የአህጉሪቷ አገሮችም አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሳሮ አብደላ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ይህ ላቦራቶሪ ለማቋቋም የምንገባው ስምምነት በላቦራቶሪው ረገድ እያደረግን ያለውን እድገት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የስፖርተኞችን በተለይም የአትሌቶችን ጤንነት በተሻለ ለመጠበቅ ከማስቻሉም በላይ ምርመራውን በውጭ ሀገር ለማድረግ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር ሲሆን የዛሬው ስምምነትም በቀጣይ ለምንሰራቸው ተያያዥ ስራዎች ሲሆን ምርመራ በማካሄድ፣ መረጃ በመለዋወጥ እና ምርምር ስራዎችን በጋራ መስራት ላይ የሚያተኩር መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ የዚህ ዓይነት የላቦራቶሪ ምርመራ የሚያከናውኑት ኬንያና ግብጽ ብቻ እንደሆኑ፣ በኢትዯጵያ የሚጀመረው ይህ ላቦራቶሪ እዚህ ለመድረስ የሚያስፈልጉ ሂደቶችን እና መስፈርቶችን ለማሟላት ወደ ከሶስት ዓመታት በላይ ወስዶበታል፣ በመጀመሪያው ዓመት 1500፣ በቀጣይ 2000 ብሎም በሶስተኛው ዓመትም እስከ 2500 ናሙናዎችን የመቀበል አቅም እንደሚኖረው እና በትግበራ ወቅትም ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ የትምህርት፣ የፍትህ፣ የስፖርት፣ የጋዜጠኞች የመሳሰሉት አካላት በሂደቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የሪፈረንስ ላቦራቶሪ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፈይሳ ጫላ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *