
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሕዳር 26/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በማርበርግ በሽታ ምንነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል ፤ በሚጠበቅባቸውም ሚና ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በመልዕክታቸው ፦የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ በመከሰቱ በነበረው ቀጥተኛ ንክኪ በሀዋሳ ከተማም አንድ ሰው ለህልፈት መዳረጉን ተከትሎ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የማርበርግ በሽታ በሀገራችን አዲስ የተከሰተ እንደመሆኑ ስርጭቱን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የሁሉንም የባለድርሻ አካላት ርብርብ ፣ቅንጅትና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ በየደረጃው የሚገኙ የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሚዲያዎች ፣በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው የበሽታውን ስርጭት በመከላከል ማህበረሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ እንዲጠብቅ የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን በማውሳት፤ የሃይማኖት መሪዎች፣ አስተማሪዎችና አገልጋዮች ምዕመናንን በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበሽታው ምክንያት ለህልፈት የተዳረገን ሰው አስከሬን የጥንቃቄ መመሪያዎችን በመከተል ክብርና ደህንነቱ የተጠበቀ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ተከትሎ ማከናወን እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
በስልጠናው ላይም የተሳተፉ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ስለ በሽታው አይነት እና የሚያደርሰውን ጉዳት እንዲሁም ማድረግ ስለሚገባቸው ስራዎች በቂ ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸውው መረጃውን ለህብተሰቡ በማድረስና ለምዕመናኑ በማስተማር የበኩላቸዉን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት
ህዳር 26/2018 ዓ.ም
ሐዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/


















































