Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የማርበርግ ቫይረስ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ የሁሉንም ዜጋ ርብርብ ይሻል አቶ በድሉ ባዴጎ።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ህዳር 30/2018 ዓ.ም

የማርበርግ ቫይረስ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ የሁሉንም ዜጋ ርብርብ እንደሚሻ የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ለሚገኙ የሀይማኖት ተቋማት በሁለት ዙር ሲሰጥ በነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ተገልጿል።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሉ ባዴጎ በመልዕክታቸው የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የበሽታ ዳሰሳና የቅኝት ስርዓቱን ማጠናከር፣ በየደረጃው በተለያዩ አማራጮች ስለቫይረሱ ግንዛቤ መፍጠር፣ ከታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና ህክምና የመስጠት ስራ እንደተሰራም አስገንዝበዋል።

ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል የሀይማኖት ተቋማት ብሎም የአጠቃላይ ማህበረሰቡ ርብርብ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

‎የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ በላይ አለማየሁ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት እንዳብራሩት ‎የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በዋናነት ከሰው ወደ ሰው በሰውነት ፈሳሽ ንክኪ አማካኝነት የሚተላለፍ፣በወረርሽኝ መልክ የሚከሰትና አንድ ሰው ለቫይረሱ በተጋለጠ ከ2 እስከ 21 ቀናት ውስጥ ምልክት የሚያሳይ አደገኛና ገዳይ በሽታ እንደሆነ ገልፀዋል።

የበሽታው ‎ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ራስ ምታት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ የሆድ ህመም እና ተቅማጥ፣ከአፍ፣ ከአፍንጫ ወይም ከተለያየ የሰውነት አካል የሚከሰት የደም መፍሰስ፣ በደረት፣ ጀርባ እና በሆድ ላይ ጎልቶ የሚታይ ሽፍታ መሆናቸውንም አስገንዘበዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ንክኪ በማስወገድና እጅን በሳሙና በተገቢው በመታጠብ ከበሽታው ተጋላጭነት ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም በማብራራት ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ ፈጥኖ ለጤና ተቋማት ማሳወቅ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

በቫይረሱ ምክነያት የሞቱ ሰዎች የቀብር ስነስርዓት አፈፃፀም እንደማንኛውም ጊዜ በሚደረግ የአስከሬን ሽኝት ሳይሆን የሞቱ ሰዎችን ደህንነትና ክብር በጠበቀ መልኩ፣ ተገቢ ስልጠና በተሰጣቸው ሰዎች እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የሀይማኖት አባቶችም የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር የማህበረሰቡን ህይወት ለመታደግ ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዉ ተከታታይነት ያለው፣ ወቅታዊና አስተማሪ መረጃዎችን ለህብተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የበኩላቸዉን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።

‎የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት

ህዳር 30/2017 ዓ.ም

ሐዋሳ

ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

Web site: https://www.sphi.gov.et/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *