
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ህዳር 30/2018 ዓ/ም
የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሀይማኖት ተቋማት በማርበርግ ቫይረስ በሽታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
የኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሉ ባዴጎ ባስተላለፋት መልዕክት የማርበርግ ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ በድሉ አክለውም ስራውን የሚመራ፣ የሚከታተል እና የሚቆጣጠር የድንገተኛ አደጋ መከታተያ ማዕከል ተቋቁሞ የምላሽ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ተይዘው ከነበሩ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች በመለየት፣ማስመርመርና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ መደረጉንና ተጋላጭነት ያላቸውን ሰዎች ለመድረስ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በዛሬው ዕለትም ከሀይማኖት አባቶች ጋር የተደረገው ውይይት ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች ወቅታዊ መረጃ ለማድረስ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ በላይ አለማየሁ በቀረበ ሰነድ ስለ በሽታው ምንነት፣ የመተላለፊያ መንገዶች፣ስለ መከላከያ ዘዴዎች ፣ በህክምና ሂደቱ እንዲሁም በቀብር አፈፃፀም ስርዓት ላይ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ማንኛውም ሰው ምልክቶቹን በራሱ፣ በቤተሰቡ እና በአካባቢው ላይ ካስተዋለ በቅርበት ላለ የጤና ተቋም በማሳወቅ፣በነፃ የስልክ መስመር 7794 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚገባ ተናግረው ምንጩ ካልተረጋገጠ ሀሰተኛ መረጃ በመቆጠብ ወረርሽኙን መከላከል እንደሚገባ ተገልጿል።
የቫይረሱ ስርጭት ሳይስፋፋ ባለበት ለመግታት ከንክኪ መቆጠብ፣ እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ( በሳኒታይዘር ማፅዳት)፣ርቀትን መጠበቅ እና ሌሎች የጥንቃቄ ዘዴዎችን መተግበር እንደሚገባ አሳስበው ፣የሀይማኖት አባቶች ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።
ከተለያዩ የእምነት ተቋማቶች የመጡ አባቶችም ስልጠናዉ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ ምዕመናኖቻቸውን በማሳወቅና በማስገንዘብ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት
ህዳር 29/2017 ዓ.ም
ሐዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/
























