
——————
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፤ የመጀመሪያው ዙር የክትባት ዘመቻም ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለብሔራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ህዳር 30| 2018 ዓ.ም በተዘጋጀው የፖሊዬ ክትባት ዘመቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት ላይ ነው::
የኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተናገሩት በመጪው አርብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚጀመረው የክትባት ዘመቻ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑና ከዚህ ቀደም ክትባቱን የወሰዱም ያልወሰዱም ህፃናት እንደሚከተቡ ገልፀዋል።
ዶ/ር መልካሙ አያይዘውም ክትባቱ ቤት ለቤት የሚሰጥ መሆኑና በዚሁ አጋጣሚ የማርበርግ ቫይረስን የመከላከል፣ ተጠርጣሪዎችን የመለየት፣ ስለ ቫይረሱ የማስተማርና ግንዛቤ የመስጠት ስራም እንደሚከናወን፤ ሌላ የጤና ችግር ገጥሟቸው በቤታቸው የተቀመጡ ህፃናትም ተለይተው ህክምና እንዲያገኙ እንደሚደረግ እናም በሌሎች ወረርሽኞች ላይ የጤና ትምህርትም እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
አቶ ግርማ ኃ/ማርያም በኢንስቲትዩቱ የስጋት ጊዜ ተግባቦት ባለሙያ እና የዘመቻው አስተባባሪ የዘመቻውን ቁልፍ መልዕክት እና በዘመቻው ወቅት ሚዲያው ሊኖረው ስለሚገባው ተሳትፎ እና የኮሚኒኬሽን ስልቶች ላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ስለፖሊዮ በሽታ እና የክትባት ሁኔታዎችን በተመለከተ ከጤና ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ገለፃ ተደርጓል።
ይህንን የክትባት ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ ለጤና ባለሞያዎች አስፈላጊው ስልጠና እንደተሰጠ፣ በክትባቱ ዙሪያ የሀይማኖት አባቶችን የማወያየት ስራዎች መሰራታቸውና እንዲሁም በድንበር ዘለል አካባቢዎች የክትባት ሳተላይት ጣቢያዎች ተቋቁመው ክትባቱ እንደሚሰጥ ከመደረኩ ለመረዳት ተችሏል።
www.ephi.gov.et/news











