Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

አንድም ህጻን በፖሊዮ በሽታ እንዳይያዝ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

———————–

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የንቅናቄ መድረክ ህዳር 29/2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አካሄደ፡፡

የንቅናቄ መድረኩ ዋና ዓላማ አሁናዊ የፖሊዮ ስርጭት እንደ ሀገር ምን እንደሚመስል ግንዛቤ ለመፍጠር ፣ ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም ለሚሰጠው ሁገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ለማሳወቅ እንዲሁም ከዚህ ክትባት ዘመቻ ጋር ተቀናጅተው ስለሚሰጡ አገልግሎቶች የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን አቶ ግርማ ኃይለማርያም የኢንስቲትዩቱ የፖሊዮ የተግባቦት ባለሙያ አብራርተዋል፡፡

አቶ እንዳለ ዘመነ በኢንስቲትዩቱ የፖሊዮና ሌሎች ወረርሽኞች ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ በመድረኩ የመክፈቻ ፕሮግራም ወቅት እንደተናገሩት የፖሊዮ ስርጭትን በተመለከተ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 41 የሚሆኑ ህጻናት በፖሊዮ በሽታ የተጠቁ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ስርጭቱን ለመግታትና ፖሊዮን ጨርሶ ለማጥፋት ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ከ25 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ክትባቱን ለመስጠት የዝግጅት ተግባራት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ፤ ክትባቱ በሁሉም ቀበሌዎች ቤት ለቤት በሚደረግ ጉብኝት በጤና ባለሙያ የሚሰጥ መሆኑን እና ሕጻናቱ ከዚህ በፊት የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይተቡም በዚህ ዘመቻ የሚከተቡ ስለመሆኑ እንዲሁም በመደበኛው የክትባት መርሃ ግብር ምንም ክትባት ያልወሰዱ ወይም ጀምረው ያቋረጡ ህጻናት የመለየትና ወደ ጤና ተቋማት የመላክ ስራን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ለህብረተሰቡ መድረስ ስለሚገባቸው ቁልፍ መልዕክቶችና ተግባራት ላይ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በመውሰድ ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

የኃይማኖት አባቶች፣ የጤና ማህበራት፣ የሚዲያ አካላት፣ የወጣቶች ማህበር ተወካዮች፣ የሴቶች እና ህጻናት ሚኒስቴር ተወካዮች በመድረኩ ተገኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡

https://ephi.gov.et/news

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *