
በሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የላቦራቶሪ አገልገሎት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ማለትም የዓለም አቀፍ መስፈርትን ለማሟላት ደረጃ በደረጃ በማሻሻል የኮከብ ዕውቅና ( ኮከብ1-4)፤በላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ ጥራት ማረጋገጫ መስፈርት (ISO-15189) መሰረት እውቅና እና በአዲስ ኮከብ ላገኙና ላሰቀጠሉ የጤና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል ።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሳሮ አብደላ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የላቦራቶሪ ዊንግ ኃላፊ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልል ላቦራቶሪዎችን አቅም ለመገንባት እና ደረጃቸውን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መቆየቱን ገልጸው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች ለላቦራቶሪ አገልግሎት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል። በመቀጠል መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ዳባልቄ ኢንስቲትዩቱ የጤናውን ሴክተር የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ዋና ዋና ተግባራትን ይዞ የህብረተሰቡን የጤና ደህንነት ለመጠበቅ እና ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ እየተከሰቱ ያሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ከሴክተር መ/ቤቶችና ከአጋር አካላትን ጋር በመቀናጀት ለሚከሰቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት መከላከል እና መቆጣጠር የሚያስችል ስራዎችን መሰራቱን ገልፀዋል፡፡
አክለውም በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ እና ፈጣን የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ዳመነ የጤና ላቦራቶሪ አዳዲስ በሽታዎችን መለየት፤ ከተለዩ በኋላ ክትትል ማድረግ እና ማህበረሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ጤና ተቋማት ላቦራቶሪዎችን ማደራጀትና ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።
መድረኩ በይፋ ከተከፈተ በኋላ አጠቃላይ የላቦራቶሪ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ማለትም ደረጃ በደረጃ የላቦራቶሪ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም(SLIPTA) እና የህክምና ላቦራቶሪ ጥራትና ብቃት( ISO 15 189:2012) ስታንዳርድ መሰረት የተሰሩ ስራዎችን የሚያሳይ ሰነድ የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት የላቦሪቶር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዳቶ አዴላ የ2017 ዓ .ም. የላቦራቶሪ ሥራዎች የአመቱን አፈጻጸም ካቀረቡ በኋላ ውይይት ተደርጎበታል። መድረኩ ውጤታማ እንደሆነ እና የተሰጠው እውቅና ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳም በተሳታፊዎች ተገልጿል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነሐሴ 24/2017 ዓ/ም
ሀዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎች የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/





















































