
———————-
በኢንስቲትዩቱ የእስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካይ አባላት፣ የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የማኔጂመንት አባላት እንዲሁም ባለሙያዎች በተገኙበት ሐምሌ 29 እና 30/2017 ዓ.ም ዓመታዊ የእቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው።
የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር፣ በላቦራቶሪ አቅም ግንባታና አገልግሎት በጥናትና ምርምር ፣ ፣ በብሔራዊ የጤና መረጃ ዙሪያ እንዲሁም በአለም አቀፍ ጤና ደንብና የአንድ ጤና በተመለከተ በዓመቱ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም የተገኙ ውጤታማ ስራዎችን ለማስቀጠል ብሎም የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው::
ወ/ሮ ወርቀሠሙ ማሞ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ የባህልና የስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ባደ ረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ለሚወጡ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቁመው፤ የግምገማ መድረኩ ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚለዩበት፣ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሰሩ ውጤታማ ስራዎች፣ ያልተዳሰሱ ስራዎች እና ክፍተቶች የሚለዩበት፣ ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራት የሚዳሰሱበት ፣ ኢንስቲትዩቱ ከተጣለበት ኃላፊነትና ከበጀት ዓመቱ እቅድ አንፃር የተመዘገቡ ውጤቶች የሚፈተሹበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መንስኤዎች የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን፣ በላቡራቶሪው ዘርፉ በሽታዎችን የመለየት ከፍተኛ አቅም መገንባቱን፣ በምርምሩ ዘርፍ በተለያዩ የጤና ችግሮች ላይ የተካሄዱ 99 የጥናትና ምርምር ውጤቶች በአለም አቀፍ ጆርናል ላይ መታተማቸውን እና የጤና መረጃዎችን የመቀመርና የመተንተን ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ፣ በአጠቃላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮች ጋር በመተባበር የተሻለ ውጤት በበጀት ዓመቱ መመዝገቡን በተመለከተ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል።
በዛሬውና በነገው ዕለት በሚከናወነው አመታዊ የስራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢንስቲትዩቱ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ ከሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ቁጥጥር አንፃር ፣ ከላብራቶሪ አቅም ግንባታ፣ ከጥናትና ምርምር ስራ ውጤቶች ፣ ከብሔራዊ የጤና መረጃ አንፃር እንዲሁም ሌሎችም በተቋሙ የተመዘገቡ ውጤቶች በሪፖርት ቀርበው በጥልቀት እየተገመገሙ ሲሆን የተመዘገቡ ውጤቶችን እና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ይታመናል::
www.ephi.gov.et/news














