Skip to content 
—————————–
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ከአፍሪካ ሀገራት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከላት መካከል በዓለም አቀፍ የጤና ደንብ አቅም መስፈርቶች መሠረት የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በቀጣይ የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የተመረጠ በመሆኑ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ አለም አቀፍ አጋር ደርጅቶች እና የክልል ጤና ቢሮና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ የልህቀት ማዕከሉን ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር የፕሮግራሙን የማጠቃለያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ዝግጁነትና ምላሽ እንዲሁም በድንበር ኬላዎችና በመላው የሀገሪቱ ክልሎች የሕብረተሰብ የጤና በርካታ ስራዎችን በመስራት የጠነከረ ምላሽ መስጠቱን ጠቁመው በኮቪድ-19 እና ሌሎች ወረርሽኞች ወቅት ከተማርነው የዝጁነትና ምላሽ ስራዎች በመነሳት የተወሳሰቡ የጤና አደጋዎችን ለመቋቋም እና ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የተሻለ አገልግሎት እና ተምሳሌት ለመሆን የልሕቀት ማዕከል መገንባት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የልሕቀት ማዕከል እንዲሆን መመረጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የዝግጁነት፣ የምላሽ አሰጣጥና የመልሶ ማቋቋም ስርዓቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ተቋሙ በአፍሪከ ካሉት ዕድሜ ጠገብ ብሔራዊ ኢንስቲትዩቶች መካከል አንዱ መሆኑን፣ በአሁኑ ሰዓት ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባራት በዝርዝር ጠቁመው፤ ለተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ በተለይም ውስብስብ የሆኑ ተደራራቢ ወረርሽኞችን በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከላት በመላው ሀገሪቱ በማደራጀትና በመምራት በቂ ምለሽ ሲሰጥ መቆየቱ፣ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የታለመውን ህልም ለማሳካት በተደራጀ የሰው ሃይል በተቀላጠፈ ቴክኖሎጂ ወደፊት ለሚጠበቀው ወሳኝ ምዕራፍ መሠረት የጣለ መሆኑን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላላፉበት ወቅት እንደገለፁት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበርያ ማዕከል በ2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተዋቀረ ጊዜ ጀምሮ የዓለም አቀፍ የጤና ህግጋት መስፈርቶች በማሟላት በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ እንደነበረ በመጥቀስ የልሕቀት ማዕከል ዓላማው በመሠረታዊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አቅም ለማጎልበት በዲጂታል የጤና መረጃ ላይ የተመሰረተ የአቅም ግንባታ ስራዎችን የማከናወን እና ቀጣይነት ያለው ብቁ የጤና ሰራዊት በመገንባት የተቀናጀ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ማዕከል ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በነበረው የማስጀመሪያ ፕሮግራም መድረክ ላይ የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮች የልሕቀት ማዕከሉን አስመልክቶ የየራሳቸውን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት እንዲሁም የተቋሙንና የማዕከሉን ታሪካዊ ሂደት አውደርዕይ ተካሂዷል፡፡
- by admin
- on September 17, 2025
0