Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

በህገ ወጥ የመድሃኒት ዝውውር ላይ ተሰማርተው ህብረተሰቡን ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጉ ያሉ አካላትን በጋራ ርብርብ መከላከል እንደሚገባ ተገለፀ።

በህገ ወጥ የመድሃኒት ዝውውር ላይ ተሰማርተው ህብረተሰቡን ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጉ ያሉ አካላትን በጋራ ርብርብ መከላከል እንደሚገባ በዛሬው ዕለት ከግል የጤና ተቋማት ባለቤቶች ጋር የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለማረም በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ ተጠቁሟል።

የሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገ/ግ/ጥ/ቁ/ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ በመልዕክታቸው በክልሉ ከ1400 በላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የጤና ተቋማት እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በክልሉ በትክክኛ መንገድ የህዝብን የጤና ተጠቃሚነት በማስቀደም እየሰሩ ላሉ የግል የጤና ተቋማት ምስጋናቸውን በማቅረብ በህገ ወጥ የመድሃኒት ዝውውር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን ግን ባለስልጣኑ እንደማይታገስ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በክልሉ የጤና አገልግሎትን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ አገልግሎቱን ስታንዳርዳይዝ ማድረግ ይገባል ሲሉ ጠቁመው ለዚህም የቁጥጥር ስርዓቱን ይበልጥ ማጠናከር እጅግ ወሳኝ ነው ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

በክልሉ በ102 መድሃኒት ችርቻሮ ተቋማት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ቁጥጥር 16 የመድሃኒት ችርቻሮ ተቋማት ጥራታቸው እና ደህንነታቸው እንዲሁም ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ ህገ ወጥ መድሀኒቶችን ይዘው በመገኘታቸው ህጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን በዚህም 564,000 ብር በላይ የሚገመት ሕጋዊ ደረሰኝ የሌላቸው የፕሮግራም መድሃኒቶች መያዛቸውን ጠቁመዋል::

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የማህበረሰብን የጤና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በታማኝነት፣ በቁርጠኝነት እና በተጠያቂነት መንፈስ ማገልገል ሲቻል እንደሆነ ጠቁመው በዚህም ላይ የመንግስትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩና ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ጤናና ጤና ነክ አገ/ግ/ጥ/ቁ/ ባለስልጣን የቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አማረ ይተራ በቁጥጥሩ ከተገኙ ህገ ወጥ ድርጊቶች መካከል ቴክኒካል ባለሙያ በስራ ገበታ ላይ አለመገኘት፣ያልተመዘገቡ ባለሙያዎች ቀጥሮ ማሰራት፣ባለሙያ ያልሆኑ ግለለቦች መድሀኒት እንዲሸጡ ማድረግ፣ህጋዊ ደረሰኝ የሌላቸውን እና የፕሮግራም መድሀኒቶች ፣የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ ከደረጃ በላይ የሆኑ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ መድሀኒቶችን ይዞ መገኘት እና መርፌ መውጋትን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን ደርቦ መስራት ለአብነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተው፤

በክልሉ በ26 የመድሀኒት ችርቻሮ ተቋማት ፣በ14 መካከለኛ ክሊኒኮች ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ፣ በ16 መድሃኒት ችርቻሮ ተቋማት ላይ ከ3ወር እስከ 1አመት ፈቃዳቸው እንዲታገድ፣ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ክልኒክ ላይ ፈቃድ እስከመሰረዝ እርምጃ መወሰዱን ባቀረቡት ሰነድ ገልጸዋል ፡፡

በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደቡብና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ የግል ጤና ተቋማት ከግል መድሀኒት አስመጪዎች ላይ በሚያገኙት አገልግሎት ምን ያህል ረክተዋል የሚለውን የሚያስረዳ የዳሰሳ ጥናት በመ/ቤታቸው እንዲቀርብ በማድረግ ያለውን ጉድለት አመላክተዋል።

የጥቅም ትስስር ያለበት የመድሀኒት ግዢና አስተዳደር ከስርቆት የፀዳ መሆን የሚችለው በመንግስት የጤና ተቋማት ውስጥ ያለው የአሰራር ሂደት ሲጠናከርና መድሀኒቶች በተዘረጉ የቁጥጥር ስርዓቶች ማለፍ ሲችሉ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ በ400 ተቋማት ላይ ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ከክልሉ ጋር ተቀናጅቶ በተሰራው ስራ እየተሻሻሉ የመጡ ነገሮች ቢኖሩም ህገወጥነትን ጨርሶ ማስቆም የሚቻለው ለህሊና በመስራት፣ የጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ይበልጥ በማጠናከርና በየደረጃው ለሚመጡ ጥቆማዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት መሆኑን አስረድተው መ/ቤታቸው ለሚመጡ ጥቆማዎች ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የሲዳማ የግል የጤና ተቋማት ማህበር በበኩሉ የተጣለበትን ሀላፊነት ለመወጣት እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት ገልፀው

የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት የቁጥጥር ዘርፉን በመደገፍና ተቀናጅተው ርብርብ በማድረግ የከፋ የጤና ጉዳት ሳይደርስ ህገ ወጥነትን መቆጣጠር እንዲቻል ተናቦ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል ።

የምክክር መድረኩ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን በአግባቡ በመምራት የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ታላሚ ያደረገ እና በየደረጃው በጉድለት ለተለዩ ተግባራት ችግር ፈቺ ሀሳቦች የተንፀባረቀበት በመሆኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተቀራርበን እንስራ ሲሉ ከሀዋሳ ከተማና ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተገኙ የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች ጠይቀዋል።

የሲዳማ ክ/መ/ጤና ቢሮ

መጋቢት 15/2017 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *